unfoldingWord 29 - የምሕረት የለሹ ባሪያ ታሪክ
ዝርዝር: Matthew 18:21-35
የስክሪፕት ቁጥር: 1229
ቋንቋ: Amharic
ታዳሚዎች: General
ዓላማ: Evangelism; Teaching
Features: Bible Stories; Paraphrase Scripture
ሁኔታ: Approved
ስክሪፕቶች ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም እና ለመቅዳት መሰረታዊ መመሪያዎች ናቸው። ለእያንዳንዱ የተለየ ባህል እና ቋንቋ እንዲረዱ እና እንዲስማሙ ለማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከል አለባቸው። አንዳንድ ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላቶች እና ጽንሰ-ሐሳቦች የበለጠ ማብራሪያ ሊፈልጉ ወይም ሊተኩ ወይም ሙሉ ለሙሉ ሊተዉ ይችላሉ.
የስክሪፕት ጽሑፍ
አንድ ቀን ጴጥሮስ ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስ፣ “ሰባት ጊዜ አይደለም፣ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ” አለው። ኢየሱስ ይህን ሲል ሁልጊዜ ይቅር ማለት አለብን ማለቱ ነው። ከዚያም ኢየሱስ ይህን ታሪክ ተናገረ።
ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት ባሮቹን ሊቈጣጠር የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። ከባሮቹ አንዱ የ10,000 መክሊት የሚያክል ከፍተኛ ዕዳ ነበረበት።”
ባሪያው ዕዳን መክፈል ስላልቻለ፣ ንጉሡ፣ “ዕዳውን ይከፍል ዘንድ ይህን ሰውና ቤተ ሰቡን ሽጡአቸው” አለው።
“ባሪያው በንጉሡ ፊት በጉልበቱ ወደቀና፣ ‘እባክህን ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ አለው። ንጉሡ ለባሪያው አዘነለት፣ ዕዳውንም ሁሉ ሰረዘለትና እንዲሄድ ለቀቀው።”
“ነገር ግን ባሪያው ከንጉሡ ዘንድ በወጣ ጊዜ፣ የአራት ወር ደመወዝ የሚሆን ዕዳ ያለበትን ባልንጀሮቹ ከሆኑት ባሪያዎች አንዱን አገኘ። ባሪያው ባልንጀራው የሆነውን ባሪያ ያዘውና፣ ‘ዕዳህን ክፈለኝ!’” አለው።
“ባልንጀራው ባሪያ በጉልበቱ ወድቆ፣ ‘እባክህን ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ አለው። ነገር ግን በዚህ ፈንታ ያ ባሪያ ባልንጀራ ባሪያውን ዕዳውን እስኪከፍለው ድረስ በወኅኒ ጣለው።”
“ሌሎች ባሮችም የሆነውን ነገር ዐይተው እጅግ ተረበሹ። ወደ ንጉሡ ሄደውም የሆነውን ነገር ሁሉ ነገሩት።”
“ንጉሡ ባሪያውን ጠራና፣ ‘አንተ ክፉ ባሪያ! ስለ ለመንኸኝ ዕዳህን ተውሁልህ። አንተም ይህንኑ ማድረግ ይገባህ ነበር’ አለው። ንጉሡ በጣም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ክፉውን ባሪያ በወኅኒ ጣለው።”
ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ይቅር ካላለ፣ እንዲሁ ደግሞ የሰማይ አባቴ ያደርግባችኋል።”